Tuesday, June 12, 2012


ታቦት ምንድነው? ለምንስ ለታቦት ይሰገዳል? ታቦት በማን ይሰራል?

ታቦት ምንድነው?

ታቦት ማለት ማደሪያ ማለት ነው። የማን ማደርያ ለሚለው ደግሞ የእግዚዓብሔር ማደሪያ ማለት ነው።
እንግዲ መልሳችንን ስንሰጥ ትክክለኛ ለመሆኑ ማረጋግርጫችን መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ የተወሰኑ ስለታቦት የተጠቀሱ ጥቅሶችን እያየን ወደፊት እንሄዳለን። ኦሪት ዘጸአት 31-33 ብንመለከት ሙሴ የእስራዔልን ህዝብ ከግብጽ ምድር አውጥቶ ወደ ከነዓን ወደ አባቶቻቸው አገር እየወሰዳቸው ሳለ ብዙ ጊዜ ከእግዚዓብሔር ጋር እንደተነጋገረ ሁላችንም እናውቃለን። እንዲሁ ሙሴ ከእግዚዓብሔር ጋር ሊነጋገር ወደ ተራራ ወጣ። ተራራዉም ላይ ሲወጣ ህዝበ እስራኤልን ከተራራው በታች ትቶአቸው ነበር። ሙሴም ተራራው ላይ 40 እና 40 ለሊት ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቆየ። እግዚአብሄርም ለሙሴ አስርቱን ትዕዛዛት በ2 ጽላቶች ላይ ቀርጾ ሰጠው። እዚህ ጋር የመጀመሪያው ታቦት ቀራጭ እግዚአብሄር እንደሆነ መጽሃፍ ቅዱስ ይነግረናል። 

ጠቃሚ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች 

ኦሪት ዘጸአት 32፥15 :-  ” ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ።”
ኦሪት ዘጸአት 32፥18 :- ”እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው።”
ክዚህም በኋላ ሙሴ ከተራራው ላይ ጽላቶቹን ከእግዚዓብሔር ተቀብሎ ሲወርድ ህዝበ እስራኤል እግዚዓብሔርኝ ክደው ጣዖት በጥጃ ምስል ሰርተው ለጣዖቱ ሲሰግዱ እና በጣዖቱ ፊት ሲጨፍሩ አይቶ ተናደደ ከእግዚዓብሔር የተቀበለዉን ጽላቶች ወደ ጣዖቱ እንደወረወረ እና ጽላቶቹ እንደተሰበሩ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ተጽፎአል።
ኦሪት ዘጸአት 32፥ 19 :- ”ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፥ ጽላቶቹንም ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበራቸው የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣቸው።
ታድያ የዘመኑ ጴንጤዎች ይቺን ጥቅስ በመያዝ። እግዚዓብሔር የሰራው ጽላት ተሰብሮአል ለዚ ታቦት ወይም ሌላ ጽላት አያስፈልግም ይላሉ   መልሱ እንደሚከተለው ነው።
ኦሪት ዘጸአት 34፥1 :-  ”እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ።
እናም ይህ ጥቅስ ሰዎች ጽላትን እንዲሰሩ እግዚዓብሔር ፍቃድ እንደሰጣቸው ይነግረናል። ሙሴም እንደተባለው አደረገ ሁለት ጽላቶችን ሰራ ወደተራራም ጽላቶቹን ተሸክሞ ወጣ እግዚአብሄርም በጽላቶቹ ላይ ከእንደገና አስርቱን ትእዛዛት ጻፈባቸው። ሙሴም ከተራራው ጽላቱን ተሸክሞ ሲወርድ ፊቱ ያንፀባርቅ ነበር። 
ኦሪት ዘጸአት 34፥29 :-እንዲህም ሆነ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር።”
ኦሪት ዘጸአት 34:30 :-  ”አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ።”
የታቦትን ርዝመቱ ቁመቱን የወሰነዉም እግዚአብሄር እንደሆነ መጽሃፍ ቅዱስ ይነግረናል።
ኦሪት ዘጸአት 25:10-15 :-   እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት። ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ። መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ።”
 ኦሪት ዘጸአት 25:26:- ”በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ።እኔ የምሰጥህን መስክር ያለው ሁለቱን ጽላቶች ነው
የታቦት ጥቅም በኦሪት (ኢየሱስ ከመወለዱ) በፊት እግዚአብሄር ከህዝቡ ጋር ለመሆኑ ምልክት ነበር። በሃዲስ ኪዳን (ኢየሱስ ከተወለደባሗላ) ለኢየሱስ ክርስቶስ የስጋው እና የደሙ ዙፋን በመሆን ያገለግላል።
ታቦት ባለበት እግዚአብሄር እና ሰው እንደሚገናኙ እግዚአብሄር እንዲ ሲል ለሙሴ ነግሮታል
ኦሪት ዘጸአት  25:21 :-  ”የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።”
የእግዚአብሄር ቁጣ በእስራኤላዊያን ላይ በመጣ ጊዜ ኢያሱም ታቦት ፊት ሰግዶ እንደጸለየ መጽቅዱስ ይነግረናል።
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 7:6 :- ”ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም አለ። ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ!”

ታቦትን ጣዖት ነው ለሚሉ መልሳችን የሚከተለው ነው።

2ኛ ቆሮንጦስ 6፥16-17 :- ”ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና፧ ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? የእግዚዓብሔር ታቦትንስ በጣዖት ቤት የሚያኖር ማነው?” 
ይህን ጥቅስ የጴንጤዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብናየው ” የእግዚዓብሔር ታቦትንስ በጣዖት ቤት የሚያኖር ማነው?”  የሚለዉን ”ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? በሚል ቀይረውታል።
ሰዎች ታቦትን ይሰሩ ዘንድ ስልጣን የላቸዉም ለሚሉን መልሳችን የሚከተለው ነው::
ኦሪት ዘጸአት  37:1-9 :-
”ባስልኤልም ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ ርዝመቱም ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። በውስጥም በውጭም በጥሩ ወርቅ ለበጠው በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት። አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገለት እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኖረ። በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች ሆኑ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። ታቦቱንም ለመሸከም በታቦቱ አጠገብ ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አገባ። ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሠራ። ሁለት ኪሩቤልንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠራ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን አደረጋቸው። ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርጎ በአንድ ላይ ሠራቸው። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ሆኑ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፥ እርስ በርሳቸውም ተያዩ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ተመለከቱ።” 
ይህን ታቦት እንግዲ ሰው እንደሰራው መጽሐፍ ቅዱስ ”ባስልኤልም ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ ” ይለናል::

ታቦት በኦሪት(ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ) እንጂ አሁን አይጠቅምም ለሚሉ መልሳችን የማቴዎስ ወንጌል 5፥17ነው::
የማቴዎስ ወንጌል 5፥17 :- እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም” ብሎአል ኢየሱስ ክርስቶስ::
ኦሪት ዘጸአት 27:21 :- ”አንተም መብራቱን ሁልጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን።” ይህን ጥቅስ ስንመለከት ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን። እንጂ ኦሪት (ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪወለድ) ብቻ አይልም።

ዳዊትም ስለታቦት በመዝሙሩ እንዲህ ብሎአል
መዝሙረ ዳዊት  132:7-9 :- ”ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን። አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት። ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ”

አንድ በእግዚአብሔር ስም የሚሰራ ቤት ታቦት ሊኖረው ይገባል።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 22:19 :- ”አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ። ”

በሰማይም ታቦት እንዳለ የሚከተለውን በማለት ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ያየውን ጽፎልናል
የዮሐንስ ራእይ11:19 :-በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።”
ታቦተ ጽዮን ከሰራቻቸው ተአምራት አንድ አንዶቹ
የእግዚአብሔርን ታቦት መንካት የማይገባቸው ሰዎች አይነኩትም። ፍልስጤሞች እስራኤልን በጦርነት አሸንፈው ታቦተ ጽዮንን በማረኩ ወይም በወስዱ ጊዜ ታቦተ ጽዮን ላይ ጣዖታቸውን ”ዳጎንን” እንዳስቀመጡ እና ታቦተ ጽዮን ጣዖታቸዉን እንዳደቀቀች በመጽሃፍ ቅዱስ ተጽፎ እናገኛለን።
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 5:1 - መጨረሻው :- ” ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወሰዱ ከአቤንኤዘርም ወደ አዛጦን ይዘውት መጡ። ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አገቡት፥ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት።በነጋውም የአዛጦን ሰዎች ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር ዳጎንንም አንሥተው ወደ ስፍራው መለሱት። በነጋውም ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር የዳጎንም ራስ እጆቹም ተቈርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር የዳጎንም ደረት ብቻውን ቀርቶ ነበር። ስለዚህም የዳጎን ካህናት ወደ ዳጎንም ቤት የሚገቡት ሁሉ በአዛጦን ያለውን የዳጎንን መድረክ እስከ ዛሬ ድረስ አይረግጡም። የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደች፥ አጠፋቸውም፥ አዛጦንንና ድንበራቸውንም በእባጭ መታቸው። የአዛጦንም ሰዎች እንዲህ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ። እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ። ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ወደ እነርሱ ሰበሰቡና። በእስራኤል አምላክ ታቦት ምን እናድርግ? አሉ እርሱም፦ የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት ይዙር ብለው መለሱ። የእስራኤልንም አምላክ ታቦት ወደዚያ ተሸከሙት። ከተሸከሙትም በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በታላቅ ድንጋጤ በከተማይቱ ላይ ሆነች ከታናሹም እስከ ታላቁ ድረስ የከተማይቱን ሰዎች መታ፥ እባጭም መጣባቸው። የእግዚአብሔርንም ታቦት ወደ አስቀሎና ሰደዱት። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አስቀሎና በመጣ ጊዜ አስቀሎናውያን፦ እኛንና ሕዝባችንን ሊገድሉ የእስራኤልን አምላክ ታቦት አመጡብን ብለው ጮኹ። በከተማይቱ ሁሉ የሞት ድንጋጤ ነበርና፥ የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ እጅግ ከብዳ ነበረችና ልከው የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱ፥ እኛንና ሕዝባችንን እንዳይገድል ወደ ስፍራው ይመለስ አሉ። ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ የከተማይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ።”

ታቦተ ጽዮን ባህረ ዮርዳኖስን ለሁለት አንደከፈለች

 መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ  3:15-17 :-  ” እንዲህም ሆነ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር። እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እጅግ ሞልቶ ነበርና ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ ሲደርሱ፥ ታቦቱንም የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ በጻርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ። የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፥ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ።”
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 3:13 :- ” እንዲህም ይሆናል የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግር ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም፥ ከላይ የሚወርደው የዮርዳኖስ ውኃ ይቋረጣል እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል። ”
አንድ ዖዛ የተባለ ካህን ያልሆነ ሰው ታቦት ሊነካ ሲል መቀሰፉን መጽሐፍ ቅዱስ ያስነብበናል::
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 13:9 :- ”ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር። ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለ ዘረጋ ቀሠፈው በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።”
አሁን ታድያ ይህቺ ተዓምረኛ ታቦት (ታቦተ ጽዮን) በእግዚአብሄር ቅዱስ ፍቃድ ከ እስራኤል ወታ ወደ ቅድስት ሃገር ኢትዮጵያ እንደመጣች እና እስካሁነም ድረስ በኢትዮጵያ እንዳለች እስራኤላዊያን ሳይቀሩ ያውቃሉ።

የታቦት ክብር

ታቦት ባለበት እግዚአብሄር አለና፣ እግዚአብሄር በታቦቱ አድሮ ህዝቡን ይባርካልና ለታቦት ስግደት እና ክብር እንዲሁም ፍርሃት ይገባል። ታቦትን መዳፈር አይገባም።
ኦሪት ዘሌዋውያን 16፥2 :-  ” እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና እንዳይሞት በመጋረጃው ውስጥ በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሁልጊዜ እንዳይገባ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው።”

የእግዚአብሔርን መንበር የሚሸክሙ ኪሩቤል እና ሱራፌል በታቦትም አጠገብ እንዳሉ መጽሃፍ ቅዱስ ይነግረናል።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 8፥7:- ”ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በቤቱ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደ ነበረው ወደ ስፍራው አመጡት። ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላይ በኩል ሸፍነው ነበር። መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩ በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር በውጭ ያለ ግን አያያቸውም ነበር እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ።”
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 5፥8:-  ” ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቱ አምጥተው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች በነበረው በስፍራው አኖሩት። ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፥ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላዩ በኩል ይሸፍኑ ነበር። መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩና በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር ነገር ግን ከውጪ አይታዩም ነበር እስከ ዛሬም ድረስ እዚያ አሉ። ”
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 3፥4 :- ” በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ ብለው አዘዙ። ”


 እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በርገጥ ብዙ ሰዎች እናውቀዋለን ግን በየዋህነት ይሁን በትእቢት ወይም በድፍረት አላውቅም ለታቦት ተገቢውን ክብር ስንሰጥ አይታይም።  እግዚአብሔር ልቦናዉን ሰጥቶን የ አምላካችንን የ እግዚአብሔርን ትእዛዝ ለመፈጸም ያብቃን! አሜን። 



4 comments:

  1. kalehiwot yasemalen

    ReplyDelete
  2. ቃለ ሂወት ያሰማልን።

    ReplyDelete
  3. ቃለ ሂወት ያሰማልን።

    ReplyDelete
  4. እናመሠግናለን። ጥሩ ትምህርት ነው። በርቱ፣ ጌታ ከናንተ ጋር ይሁን።

    ReplyDelete