Tuesday, January 10, 2012

ታቦተ ጽዮን እንዴት ወደ ኢትዮዽያ መጣች?

ንጉሥ ስሎሞን እግዚአብሔር እጅግ ብዙ ጥበብ እና ማስተዋል እንደ ባህር አሸዋ የልብ ስፋት የሰጠው ጥበብ በምስራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብ እና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ ከሰዉም ሁሉ ይልቅ ጥበበኛ የነበረ በዙሪያውም ባሉ ሕዝብ ሁሉ ዝናዉ የወጣ ሦስት ሺሕ ምሳሌዎች (3ሺህ) ከ አምስት መኃልይ የተናገረ አስደናቂ ጥበበኛ ንጉሥ ነበር። በዚሁም በተሰጠው ጥበብ የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ሰርቶ በፈጸመ ጊዜ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን እንዲህ ሲል መጣ። ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት በሥርዓቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስበትም ዘንድ ትእዛዜን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባጥ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ። በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም። ብሎ ነበር። (መጽ ነገ 6፥12)  ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት (መጽ ነገ 3፥5) ዳግመኛ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ እኔ። ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከተል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለዉ ብሎ አስጠንቅቆት ነበር።  

ነገር ግን ሰሎሞን ይህን ሁሉ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ተላልፎ በሴቶች ፍቅር ተማርኮ በዝሙት ረክሶ የጣዖት ቤት ሰርቶ ጣዖታትን በማምለክ ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳይከተል ካዘዘው ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡን አርቆአልና፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ነገር አልጠበቀምና እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቈጣ። እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው። ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ሥርዓቴን አልጠበቕምና መንግሥትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ። ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም። ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልቀድም። እግዚአብሔርም ከኤዶምያስ ነገሥታት ዘር የኤዶምያስን ሰው ሃዳድን ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው።


 እግዚአብሔር ሰሎሞንን የቀደስኩትን ቤተ መቅደስ በአንተ በደል ምክንያት አጠፋዋለሁ ብሎት ነበር እና ለጥፋቱ ወይም ለቅጣቱ የሚልከው ናቡከደነጾር በሌላ ዘመን መጥቶ እስኪአጠፋው ድረስ የመረጣት ዓሠርቱ ቃላት የጻፈባቸው ሁለት ጽላት የያዘች የቃል ኪዳኑ ታቦተ ጽዮን በቀደሳት ሀገር በብሔረ አግአዚ ትኖር ዘንድ ጠባቂዋና አገልጋይዋ ሊቀ ካህናት አዛርያስ በፈጣሪው እግዚአብሔር ላመነ ለኢትዮዽያዊዉ እብነ ሐኪም ዳዊት ይህችን ታቦት እንዲያስረከበው ትእዛዙን የሚነግረው መልአክ ወደ ሊቀ ካህናት አዛርያስ ላከ።  አዛርያስ ተኝቶ ሳለ መልዕከ እግዚአብሄር በሌሊት ታየውና አራት የዓመት ፍየሎች ፣ንጹሐን የሆኑ አራት የዓመት በጎች ፣ ቀንበር ያልነካው አንድ ንጹህ ወይፈን  ሰለ ሐጥያት ስረየት ታቦተ ጽዮን ባለችበት በምስራቅዋና በምዕራብዋ በሰሜንዋ እና በደቡብዋ መድበህ አንተ እና ካህናተ እግዚአብሔር የሆኑት ወንድሞች ህ ኤልምያስ (ሊቀ ዲያቆን)፣ አቢስ ፣ ማክሪ ሁናችሁ እብነ ሐኪም (ዳግማዊ ዳዊት) ለእግዚአብሔር ቃልኪዳን ታቦት መስዋት እንዲሰዋ አባቱ ሰሎሞንን ይጠይቅ። ሰሎሞንም ይፈቅድለታል። ዳግመኛም የካህን ሳዶቅ ልጅ አዛርያስ (ሊቀ ካህናት) መስዋዕቱን ለእግዚአብሔር ይሰዋልኝ ይበለው ፣ ሰሎሞንም ይሰዋልክ ይለዋል። አንተም መስዋዕቱን ከሰዋህ በኋላም የ እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦተ ጽዮንን ከቤተ መቅደሱ ታወጣታለህ፣ ስታወጣም እንዴት እንደምታረጋት ዳግመኛ መጥቼ አሳይሀለው፣ ይህም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ነው። የእስራኤል ንጉስ ሰሎሞን እግዚአብሔርን አስቆጥቶታልና ስለዚህ እግዚአብሔር የቃልኪዳን ታቦቱን ከእስራኤል አውጥቶ ወደ ሐበሻ ሀገር ይሰዳታል ብሎ ተሰወረ። አዛርያስም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እጅግ ደስ አለው። ከዚያም ካህናት ወደሆኑት ወንድሞቹ በመሄድ ያየዉን ነገር እንዲህ ሲል አስረዳቸው፣ መልአከ እግዚአብሔር ዛሬ ሌሊት በሕልሜ እንደነገረኝ ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት (ታቦተ ጽዮን) ለሐበሻ ሕዝብ እንደምትሰጥ እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግስት እንደናቀ ታቦቲቱንም እኛ እንደምናደርሳት እዉነት ነው ፣አለ። ከዚህ በኋላ ዳግማዊ ዳዊት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንድሰዋ ፈቀድልኝ በሎ አባቱን እንዲጠይቅ አንንገረው ተባብለው አብረው ሂደው ለዳግማዊ ዳዊት ነገሩት። ዳግማዊ ዳዊትም የዩዳሔን ልጅ ኢዩአስን አስጠርቶ የደህንነት መሥዋዕት ለእግዚኣብሔር እንድሰዋ ፍቀድልኝ ይልሃል ልጅህ ብለህ  ለ አባቴ ለሰሎሞን ንገርልኝ ብሎ ላከው። የተላከዉም መልዕክተኛ የተላከበትን መልዕክት ለንጉስ ሰሎሞን አደረሰ። ሰሎሞንም በዚህ ደስ እያለው መሰውያውን እንዲያዘጋጅ ልጁም እንዲሰዋ ካህናቱን አዘዘ። ከዚያ ልጄ እንደፈለገው አድርጎ መስዋዕት ይሰዋ ብሎ ወደ አዛርያስ ካህን መልዕክት ላከ። አዛርያሰም መልዕክተኛው በነገረው ነገር ደስ አለዉና ሂዶ ከአባቱ መንጋ ቀምበር ያልነካው አንድ ወይፈን ፣ አራት የዓመት ፍየሎች፣ አራት ንጹሓን በጎች አመጣ። ዳዊትም መስዋዕት እንዲሰዋ ወደ መሰዊያው በሔደ ጊዜ አባቱ የሚሰውትን በጎች ላከለት። በዚህን ጊዘ ካህናቱ ተሰበሰቡ። አዛርያስ ካህንም መልአከ እግዚአብሔር እንደ ነገረው አድርጎ ያቀረበዉን መስዋዕት ሰዋ። ዳዊትም ባንድ በኩል መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር ሰዋ። መስዋዕቱን  ሰውተው ከፈጸሙ በኋላ ዳዊትም አዛርያስ ካህኑም ሁሉም ወደየቤታቸው ተመልሰው ተኙ። 


መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ እነሆ ዳግመኛ ለ አዛርያስ ሲታየው እሳት የመሰለ ወጥቶ ቤቱን ሁሉ አበራው። አዛርያስንም ቀስቅሶ አስነሳውና ቁም ጠንክር ወንድሞችህ ኤልምያስን ፣ አቢስን አና ማክሪን ቀስቅሳቸው የሉሕ ዕንጨትንም ወስዳችሁ ሣጥን አሰሩ ከዚያ ወዲያው ያለ ችግር የቤተመቅደሱን ደጅ አፍ እኔ እከፍትልካለው አንተም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት አንስተህ ትወስዳልህ እኔም ሁል ጊዜ ከአንተ ጋር ሁኜ እንድመራህ ከእግዚአብሔር ታዝዤአለሁ አለው። ያንጊዜ አዛርያስ ከእንቅልፉ ነቅቶ ሦስቱን ወንድሞቹን ቀሰቀሳቸው። እነርሱም ነቅተው ተነሱ አዛርያስም ታቦቲቱን የምናስቀምጥበት ሳጥን ማሰሪአ ገንዘብ እንኩ አሰርታችሁም አምጡ አላቸው። እነርሱም አዛርያስ እንዳዘዛቸው ሳጥኑን አሰርተው ወደ ቤተመቅደስ ቢሄዱ ከውጪ እስከ ውስጥ እስከ ታቦተ እግዚአብሔር አጠገብ ድረስ ደጅ አፍ ሁሉ ተከፍቶ አገኙት። ለአዛርያስ በህልም የነገረው መልአከ እግዚአብሔርም ስለሚጠብቃት ወድያው ታቦተ ጽዮን እንደ አይን ጥቅሻ ተንቀሳቀሰች። አራቱ ካህናተ እግዚአብሔር  አዛርያስ፣ ኤልምያስ፣ አቢስ እና ምክሪም ታቦተ ጽዮንን አንሥተው በሳጥን ውስጥ ቆልፈው ወስደው በአዛርያስ ቤት ውስጥ አስገቡአት። ተመልሰው ሂደዉም ታቦተ ጽዮን የነበረችበትን መንበር ገጥመው ልብስ አልብሰው ቤተ መቅደሱን ዘግተው  ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ሐር ምንጣፍ አንጥፈው መብራት እያበሩ በግ እየሰው ዕጣን እያጠኑ ሰባት ቀን ሰባት ሌሊት በአዛርያስ ቤት አሰነበቱአት። ከዚያም ከሰባት ቀን በኋላ የንጉስ ሰሎሞን ልጅ የሆነው ዳግማዊ ዳዊት ወደ ሀገሩ ወደ ኢትዮዽያ ለመሄድ በተዘጋጀ ጊዜ ወደ አባቱ ገብቶ አባቴ ሆይ መርቀህ ስደደኝ አለው። አባቱ ሰሎሞንም የልጁን ራስ ይዞ አባቴ ዳዊትን እና አብርሃምን የባረከ እግዚአብሔር አምላክ ይባርክህ እያለ ብዙ የተባረኩ አባቶቹን እነ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን ….. እየጠራ ልክ እነርሱን የባረከ እግዚአብሔር እንደነሱ ይባርክህ እያለ ብዙ ባረከው። 


ዳግማዊ ዳዊትም ተመርቆ እንደ ጨረሰ እጅ ነሰቶ ሔደ። ከዚያ በኋላ አዛርያስ እና ካህናቱ አስቀድመው ታቦተ ጽዮንን ከንዋየ ቅድሳትዋ ጋር ወርቅ ሰረገላ ላይ አስቀመጥዋት ፣ አልባሳቱንም በሌላ ሰረገላ ጫኑ። የእንቢልተኞች አለቆችም ተነስተው ቀንደ መለከት ነፉ። ከተማይቱ ጮኸች። ጎልማሶችም ደነፉ። ታቦተ ጽዮንን ግርማ ጋረዳት። የእግዚአንሔርም ግርማ ከበባት። የእስራኤል መኳንንትና ካህናት ልጆችም ለመሄድ በመነሳታቸው ሽማግሎች እሪ አሉ። ሕፃናትም ጮሁ፣ ባልቴቶች ዋይዋይ አሉ። ደናግል እያለቀሱ ተንሰቀሰቁ። ሀገሪቱ የምታለቅሰው በእነሱ መሔድ ብቻ አልነበረም፣ ግርማዋ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ስለሔደ ነው እንጂ። ንጉስ ሰሎሞንም በጭሆቱና በለቅሶው ደነገጠ። የሚሔዱ ሰዎችም ግርማ ለብሰው ባያቸው ጊዜ ታወከ ተርበደበደም። አንጀቱ ሁሉ ተገለባበጠ ዕንባው ሁሉ እስከ ልብሱ ፈሰሰ። እንዲሁም አለ ይህ የምወደው ልጄ በመሔዱ የሀገሬም ግርማ አብሮት በመሔዱ የሐርበኞቼ ልጆችም በመጓዛቸው እንግዲህ ወዮልኝ ክብሬም አልፎአል የመመኪያዬ ዘዉዴም ወድቆአል ፣ ሆዴ ተቃጠለ ከዛሬ ጀምሮ መንግስቴ ተቀምታለች። አባቴ ዳዊትም ከዚህ ቀደም ሳለ ” ኢትዮዽያዊያን በእግዚአብሔር መሢሕ ክርስቶስ ፊት ቁመው ይጸልያሉ ፣ ጠላቶቹ አይሁድ ግን ከርሰ ሲኦል ውስጥ ወድቀው መከራ አመድ ይቅማሉ። ዳግመኛም ኢትዮዽያ እጆችዋን ዘርግታ ጸሎትዋን ወደ እግዚአብሔር ታቀርባለች። እርሱ ፈጣሪዋ እግዚአብሔርም ጸሎትዋን በክብር ይቀበላል። ነገስታትዋም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። ሦስተኛም የኢሉፍሊፍ እና የጢሮስ በኢትዮዽያ የተወለዱ ህዝብ ሁሉ  እንሆ ጽዮን እናታችን ናት ይሉአታል እያለ በመዝሙር ተቀኝቶላቸዋል።” እያለ አነባ።


ከላይ የተጠቀሰው የክርስቶስ ስም ኢትዮዽያ በብሉይም ኢየሱስ ክርስቶስ ብለው በቀጥታ የጌታችንን እና የመድሃኒታችንን የ ኢየሱስ ክርስቶስን ስም የሚጠሩ መጽሃፍት ባለቤት እንደሆነች እና ክርስቶስን በብሉይም ታውቀው እንደነበር ያስረዳናል።


ዳግማዊ ዳዊት ወደ ሀገሩ ወደ ኢትዮዽያ በሚመለሰበት ጊዜ እርሱ ሳያውቅ ታቦተ ጽዮንን አጅበው ነበርና መለከ እግዚአብሔር ቅዱስ ሚካኤል ሰይፉን እንደመዘዘ ከፊት እየመራቸው መንገዳቸዉን አቅንተው በሰላም ተጓዙ። ልክ ተከዜ ባህር ጋር እንደደረሱ ቅዱስ ሚካኤል ክንፉን ዘርግቶ ባህሩን እንደ ደረቅ መሬት አድርጎ አሻገራቸው።  እንዲሁ መላዕኩ እየረዳቸው የ 13 ቀን መንገድ በአንድ ቀን ደርሰው የአባይ ዉሃ (ተከዘ ውሃ) አጠገብ ሰረገላዎቻቸዉን አዉርደው አረፉ። 


በመንገዳቸው ድንቅ ተአምር ከሚያዩ ወገን የሆኑ ምሁራን ከጌታቸው (ከዳዊት)ፊት ቁመው ህዝቡን ሁሉ ሰብስበው አንዲት ነገር እንንገረክ አሉት። እርሱም ንገሩኝ አላቸው። እነርሱም ከሰማይ ፀሐይ ወርዳ በሲና ላይ ለሙሴ ተሰጠች ከሙሴም እስከ አሤይ ዘር ድረስ ለዳዊት ወገን መድሃኒት ሆና ነበር። የህችም የእግዚአብሔር ትእዛዝ ዓሥሩ ቃላት የተጻፈባቸው ሁለት ጽላት የያዘች ታቦተ ጽዮን ናት። እነሆ አሁን በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንተ መጣች ፣ ይህ የሆነው ከእኛ አይደለም በፈጠረው እና በሰራው በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ እንጂ እኛ አሰብን እግዚአብሔር ፈፀመው አሁንም እግዚአብሔር  አንተን መረጠ የተቀደሰች ሰማያዊት የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን የታቦት መልዕክተኛ ትሆን ዘንድ ሀገርህን ወደደ። ይህቺም ለአንተ እና ለዘርህ ከአንተ በኋላ ለሚጠሩ ለልጅ ልጅህ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ መሪት ሁንህ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ ፈቃዱንም ብትፈጽም ታቦተ ጽዮን ካለችበት መንበር አትንቀሳቀሰም። አዛርያስ ይህን እንደተናገረ። ዳግማዊ ዳዊት ሁለት እጆቹን ልቡ ላይ አድርጎ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ ንጹህ ማደሪያህ የሆነች የቀደስካትን ታቦተ ጽዮንን በአይኔ አያት ዘንድ በውኑ በይቅርታህ አስበኸኛል እያል  ጸለየ። ከዚያም ሁሉ ምስጋና በኋላ እንደ ጥጃ እየዘለለ ተነሣ።

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖቴ ምንጭ ክብረ ነገስት

ቀጣዩን የታቦተ ጽዮንን አመጣጥ በቅርብ ቀን ይጠብቁ
. ዳግማዊ ዳዊት ታቦተ ጽዮንን እንደተሳለመ እና በፊትዋም እንደጸለየ 
.የኢትዮዽያ ሰዎች እንዴት ታቦተ ጽዮንን ተቀበሉአት
.ንጉስ ሰሎሞን ታቦተ ጽዮን እንደጠፋች እንዳወቀ

No comments:

Post a Comment