Wednesday, December 21, 2011

በ አንድ ቀን ውስጥ የተመደቡ የጸሎት ጊዜያት


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ዓሃዱ አምላክ አሜን
በ አንድ ቀን ውስጥ የተመደቡ የጸሎት ጊዜያት

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስርዓት መሰረት አንድ ቀን ውስጥ የተመደቡ የጸሎት ጊዜያት ሲኖሩ እነርሱም ሰባት ()ናቸው አንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው ቢችል አንድ ቀን ዉስጥ  ሰባቱንም ጸሎታት ማድረስ ይኖርበታል፣ በስራ ወይም በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ሳይመቸው ቢቀር ቢያንስ በጸሎቱ ሠዓታት ሚታሰቡትን ነገሮች አስቦ ማሳለፍ ይኖርበታል። ነገር ግን እናመሰግነው ዘንድ ለፈጠረን አምላክ በስራስ ቦታ ቢሆን የሁለት እና የሦስት ደቂቃ ጊዜ እነዴት እናጣለታለን? እና ከቻልን አቡነ ዘበሰማያት (አባታችን ሆይ) የምትለዋን አጭር ጸሎት ብናደርስ ይመረጣል። ያንንም እናደርግ ዘንድ እግዚአብሄር ይርዳን !

ከቀኑ የመጀመርያው ጸሎት የንግህ ጸሎት ” የሚባል ሲሆን እርሱም ከንጋቱ አንድ (፩) ሠዓት ገደማ የሚጸለይ ጸሎት ነው። ይህን የንግህ ጸሎት ስንጸልይ፦ የለሊቱን ጨለማ አርቀህ በሰላም የቀኑን ብርሃን ያመጣህልን ወይም ያሳየኸን አምላክ ተመስገን በማለት፣ የሁሉ አባት አዳም የተፈጠረበትን ሠዓት እና ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዺላጦስ ፊት ቆሞ የተመረመረበትን ሠዓት በማሰብ እና በማስታወስ የሚጸለይ ጸሎት ነው።

ሁለተኛዉ ጸሎት ደግሞ የሦስት ሠዓት” ጸሎት የሚባል ሲሆን ይህን ጸሎት ስንጸልይ፦ የሁሉ እናት ሄዋን የተፈጠረችበት ሠዓት፣ ነብዩ ዳንኤል በምርኮ በሚኖርበት በባቢሎን ሳለ በእየሩሳለም አቅጣጫ ያለዉን መስኮቱን ከፍቶ የጸለየበት ሠዓት፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመላዕኩ ከቅዱስ ገብርኤል ሠማያዊ ብስራት የሰማችበት ሠዓት፣ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት የተገረፈበት ሥዓት እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ በጵርሐ ፅዮን በሐዋርያት ላይ የወረደበት ሠዓት ስለሆነ እነዚህን ድርጊቶች እና ሰዓቶች በማሰብ የሦስት ሠዓቱን ጸሎት እናደርሳለን።

ሦስተኛዉ ጸሎት  የስድስት ሠዓት ጸሎት”  የሚባል ሲሆን። በቀትር ከፀሀይ ሙቀት የተነሳ ሰውነት ሲዝል ሃሳብ (አእምሮ) ሲበተን አጋንንት ስለሚሰለጥኑ ያንን የመናፍስት ጦር ለመከላከል በተለይም ጊዘው
-ሄኖክ ቤተመቅደስ ያጠነበት
-ይልቁንም ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ሲል በቀራንዮ አደባባይ የተሰቀለበት ሠዓት ስለሆነ ህማማተ መስቀሉን እያሰብን የምንጸልየው ጸሎት ነው።

አራተኛው ጸሎት ደግሞ የዘጠኝ ሠዓት” ጸሎት ይባላል። ይህቺ ሠዓት መላዕክት የሰውን ምግባር እና ፀሎት የሚያሳርጉባት ከዚያም በላይ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ሳለ  ጎኑን በጦር ተወግቶ ደሙን ከማፍሰሱ በፊትተፈፀመ” ብሎ ነፉሱን ከስጋው የለየባት ሠዓት ስለሆነች፣ ይህንንም ስለ እኛ ሲል ማድረጉን (ስለ እኛ  ሲል ነፍሱን መስጠቱን እያሰብን) የምንጸልየው ጸሎት ነው።

አምስተኛዉ ጸሎት ”የሰርክ ጸሎት ሲሆን ከ 11-12 ሠዓት ባለው ጊዜ ዉስጥ ይጸለያል። ሰው ሲሰራ ውሎ ዋጋዉን ወይም የእለት አበሉን የሚቀበለው በሰርክ አንደመሆኑ ምዕመናንም ምግባረ ትሩፋታቸዉን ሲሰሩ ኖረው ዋጋቸዉን ከፈጣሪያቸው የሚያገኙት በዕለተ ምፅዓት ስለሆነ የሰርክ ጸሎት በጌታ ዳግም ምጽሃት ይመሰላል። እንዲሁም ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህማማተ መስቀሉን ጨርሶ ከተገነዘ በሗላ በስጋ ወደ መቃበር የወረደበት ሠዓት ስለሆነ ያን የመለኮት ፍቅር በማሰብ በጸሎት የምንጠመድበት ጊዜ ነው።

ስድስተኛው ጸሎት የማታ ጸሎት” ይባላል። ይህም ጸሎት ከመኝታ በፊት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ ይጸለያል። ፈጣሪያችን በቸርነቱ የቀኑን ድካም አሳልፎ የለሊቱን እረፍት ስላመጣልን እያመሰገንን፣ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሽተ ሐሙስ በጌቴሲማኒ በአትክልቱ ቦታ ስለጸለየው ጸሎት እና በዚያን ጊዜ ስለ እኛ ሲል በጭንቀት ከእኛ የሞትን ፍርሃት አስዎግዶልን የዘለዓለም ደስታን እና ህይወትን ያቀዳጀን መሆኑን በማሰብ ለእርሱ ምስጋናችንን ከማቅረብ ጋር የሚጸለይ ጸሎት ነው።

ሰባተኛው እና የመጨረሻው ጸሎት ”የእኩለ ለሊት” ጸሎት የሚባል ሲሆን ከለሊቱ ስድስት (6) ሠዓት ላይ የሚጸለይ የምስጋና ጸሎት ነው። ሠዓቱ ጳውሎስ እና ሲላስ በእስርቤት ሣሉ ጸልየው በእግዚአብሔር ሀይል ከእስራታቸው የተፈቱበት፣ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት እንዲሁም ሞትን ድል ነስቶ የተነሳባት ዳግመኛም በህያዋን እና በሙታን ለመፍረድ የሚመጣባት ሠዓት ስለሆነች ይህን ሁሉ በማሰብ እና እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ያደረገዉን ነገር ሁሉ በማሰብ የሚጸለይበት ሠዓት ነው።
ይቆየን ወስብሃት ለእግዚሃብሔር
ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖቴ
http://ethiopianortodox.blogspot.com/

1 comment:

  1. ጸሎት ከምግብ ቡሃላ ና በፊትስ ?

    ReplyDelete